የመምፈስ የሕይወት ምንጭ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን
MEMPHIS SPRING OF LIFE EVANGELICAL CHURCH
Abesha
Amharic
Ethiopian
protestan
tMemphis
የመምፈስ የሕይወት ምንጭ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን የእምነት መግለጫ
-
ስድሳ ስድስቱን የብሉይና የአዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት የያዘው መጽሐፍ ቅዱስ በሙሉ የእግዚአብሔር እስትንፋሳዊ ቃል ፤ፍጹም የሆነና የቤተ ክርስቲያን እምነት ፤ሥርዓት፤ መሠረትና ሥልጣን እርሱ ብቻ መሆኑን ታምናለች።
-
መንፈስ የሆነው እግዚአብሔር ዘላለማዊ፣ሁሉን ቻይ ፣የሰማያትና የምድር በውስጣቸውም ያለውን ሁሉ የፈጠረ፣ የማይወሰን፣ የማይለወጥ፣በራሱ ማንነት የሚኖር ራሱን በሶስት አካል ማለትም በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ በገለጠው በአንድ አምላክ ታምናለች።
-
እግዚአብሔር አብ ከዘለዓለም ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለ የነበረና የሚኖር የኢየሱስ ክርስቶስ የእስራኤልና የአማኞች ሁሉ አባትና አምላክ መሆኑን ታምናለች።
-
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር አብ የወጣና በመንፈስ ቅዱስ ተጸንሶ ከድንግል ማሪያም የተወለደ ፍጹም ሰውና ፍፁም አምላክ መሆኑን ፤ዓለማትን ሁሉ መፍጠሩን፣ ሰውን ለመዋጀትና ከእግዚአብሔር ጋር ለማሰታረቅ ራሱን ቤዛ አድርጎ በመስቀል ላይ መሞቱን፣ በሶስተኛው ቀን ከሙታን መነሳቱን ፣ወደ አብ ቀኝ በክብር ማረጉን ፣ አሁን ለእኛም እየማለደ ዘወትር በሕይወት የሚኖር የቤተ ክርስቲያን መሥራችና ራስ መሆኑንና ለፍርድም በክብርና በማዕርግ ተመልሶ እንደሚመጣ ታምናለች።
-
መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ የሠረፀ ምልዓተ አካል ያለው ፍጹም መለኮት፣የእውነት መንፈስ፤ አፅናኝ ፤የኢየሱስ ምስክርና ስለ ኃጢአት፣ ስለጽድቅና ስለፍርድ ዓለምን የሚወቅስ፣ በአማኞች አድሮ ወደ እውነት ሁሉ የሚመራቸው፣የሚያስተምራቸው፣የሚያሳስባቸው ፣ ልዩ ልዩ የፀጋ ሥጦታዎችን ለአማኞች እያካፈለ በሙሉ ኃይልና ሥልጣን አገልግሎቶችን በመፈጸም ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ለእግዚአብሔር መንግሥት መስፋፋት፣ ለቤተ ክርስቲያን መታነጽ እንደሚሠራ እንዲሁም የመጀመሪያይቱ ቤተክርስቲያን ልምምድ የሆነውን በመንፈስ ቅዱስ ሙላትና ጥምቀት በአዲስ ልሳንም መናገር ታምናለች።
-
የውሃ ጥምቀት በቀጥታ በኢየሱስ ክርስቶስ ከዚያም በሐዋርያትና በቅዱሳን የታዘዘ በመሆኑ፤ በጸጋው በእምነት ደኅንነታቸውን የተቀበሉ ሁሉ በልባቸው ያመኑትን በገሃድ የሚመሠክሩበት ፣ሞቱን በሚመስል ሞትና ትንሣኤውንም በሚመስል ትንሣኤ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መተባበራቸውን በውሃ በመጠመቅ ( ሙሉ በሙሉ ውሃ ውስጥ ጠልቀው በመግባትና በመውጣት)፣ ለኃጢአት ሞተው በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ሆነው ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደሆኑና የእግዚአብሔር ቤተሰብ እንዲሁም የኢየሱስ ክርስቶስ አካል እንደሆኑ ራሳቸውን የሚቆጥሩበትና የሚያውጁበት ሥርአት መሆኑን ታምናለች።
-
የጌታን እራት የምንካፈለው ጌታ ኢየሱስ በቀራንዮ በምትካችን ሆኖ የከፈለልንን የኃጢአት ዕዳ ለማሰብና ጌታ ተመልሶ እስኪመጣ ድረስም ሞቱን ለመናገር ከጌታ የተሰጠ ትዕዛዝ መሆኑን፣ የምንበላው እንጀራ የተቆረሰው የክርስቶስ ሥጋና የምንጠጣው ጽዋ ለበዙዎች የፈሰሰው የኢየሱስ ክርስቶስ የአዲስ ኪዳን ደም ለማሰብ መሆኑንና ከጌታም ጋር ኅብረት የምናደርግበት መሆኑን የሚያመለክት ስለሆነ ምዕመናን የጌታ ሥጋና ደም ባለዕዳ እንዳይሆኑ በማስተዋልና በመረዳት የሚካፈሉበት ክቡር ሥርዓት መሆኑን ታምናለች።
-
ክርስቶስ በደሙ የዋጃት አካሉ በሆነች ከእግዚአብሔር መንፈስ ዳግም የተወለዱ አማኞች ሁሉ በሚገኙባት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታምናለች ።